ኢንቪትሮ ፈርትላይዜሽን (IVF) ምን ማለት ነው
- እንዴት ነው እርግዝና ወይም ፅንስ በተፈጥሮአዊ መንገድ የሚፈጠረው
አንድ ሴት እንድታረግዝ የግድ የወንድ ዘር ከብልቷ በማህጸን ጫፍ (ከበታች የሚገኘው ጠባብ የማህጸን ክፍል) አልፎ ወደ ማህፀን ውስጥ ከዛም ወደ አንደኛው የማህፀን ቱቦ መግባት አለበት ፡፡ የወንዱ ዘር ወደ ማህጸን ቱቦ ከደረሰ በኋላ እንቁላል ከእንቁልጢ (ovary) ተለቆ ወይም ተፈልፍሎ ተገናኝተው (አብዛውኛውን ጊዜ እንቁላል በተለቀቀበት በኩል ባለው ቱቦ) ፅንስ ይፈጥራል ፡፡
አይ. ቪ.ኤፍ ምንድ ነው (IVF)
አይ.ቪ.ኤፍ ማለት የወንዱ ዘር እና የሴቷን እንቁላል አውጥቶ ከማህፀን ውጪ በላብራቶሪ ውስጥ እንዲዋሃዱ የሚደረግበት በህክምና የታገዘ የስነ ተዋልዶ ዘዴ ነው ፡፡
በላብራቶሪ ውስጥ የተፈጠረው ፅንስ በሚፈለገው ደረጃ እድገቱን ከቀጠለ በኋላ ወደ ሴቷዋ ማህፀን በማስገባት የተፈጥሮ እርግዝና ሂደቱን እንዲቀጥል የሚደረግ ይሆናል፡፡
አይ.ቪ.ኤፍ አገልግሎት የሚሰጣቸዉ እነማን ናቸዉ?
ጥናቶች እንደሚያመለክቱት የአይቪኤፍ አገልግሎትሊደረግላቸዉ የሚችሉ ሰዎች እድሜያቸዉ ከ 35 አመት በታች እና ልጅ ለመዉለድ ቢያንስ ለአንድ አመት ያክል ምንም አይነት የእርግዝና መከላከያ ሳይወስዱ ሞክረዉ እርግዝና ያልተሳካላቸዉ ባለትዳሮች መሆን አለባቸዉ፡፡ አንዳንዴም ከዚያ በላይ ለተጨማሪ 6 ወር በላይ ለሞከሩም ሊሰራ ይችላል::
የእድሜ መጨመር የፅንስ የመፈጠር እድሉን ሊያጠበዉ ስለሚችል እድሜያቸዉ ከፍ ላሉ ታካሚዎችን የመፀነስ እድሉን ላለማጣት ሂደቱን ቶሎ እንዲጀምሩ ይደረጋል፡፡
በአይቪኤፍ ህክምና አገልግሎት ሊፀነስ የሚቻልባቸው ዋናዋና የመካንነት ችግሮች
- ጤናማ እንቁላል የማምረት ሂደት ችግር
- የተዘጋ የማህፀን ቱቦ
- ጤናማ ያልሆነ ማህፀን
- የወንድ የዘር ፍሬ ቁጥር ማነስ
- ጤነኛ ያልሆነ የወንድ የዘር ፍሬ እንዲሁም ሌሎች የወንድ የዘር ፍሬ ችግሮች
መሰረታዊ የአይቪኤፍ ሂደቶች
- ኦቫሪ እሰቲሙሌት ማረግ (Ovary Stimulation)
- ለተጠቀሰዉ ህክምና አስፈላጊ የሆኑ መድሃኒቶችን ማዘዝ
- መድሀኒቶቹ ሆርሞኖቹን አነቃቅቶ እንቁላል ማምረት እና ብዙ እንቁላሎች እንዲመረቱ ማድረግ
- በአልትራሳውንድ በመታገዝ የእንቁላሎችን እድገትና የደም ናሙና በመዉሰድ የሆርሞኖችን ይዞታ መከታተል
- ከ 10-12 ቀናት በሁዋላ እንቁላሎቹ ሊወሰዱ ዝግጁ ማድረግ
- ያላደጉት እንቁላሎች ፈሳሽ በተሞሉ ከረጢቶች ዉስጥ በሴትዋ ማህፀን ይገኛል ፤ ሆርሞኖቹ ፅንሱ እድገት እንዲያገኙ የሚረዱ ሲሆኑ እነዚህን ሆርሞኖች ማነቃቂያ የምንሰጣቸዉ መድሀኒቶች ሰዉነታችን በተፈጥሮ ከሚያመርታቸዉ ሆርሞኖች ጋር ተመሳሳይ አገልግሎት የሚሰጡ ናቸዉ፡፡
- የእንቁላል የማዉጣት ሂደት
የተሳካ አይቪኤፍ የሚባለዉ ያኮረቱ ከአንድ በላይ እንቁላሎች ሲወሰዱ ነዉ፡፡ የህክምናዉ ባለሞያ ቀጭን መርፌ የመሰለ መሳሪያ በመጠቀም ወደ ሴትዋ ብልት በመግባት ከሴትዋ እንቁልጢ (Ovary) ያኮረቱትን እንቁላሎች ይወስዳሉ፡፡ በዚ ሂደት ቁጥራቸዉ የበዛ እንቁላሎች ሊገኙ ይችላሉ፤ ሀኪሙ እንቁላሎቹን የሚያወጣበት ዘዴ አስቸጋሪ ወይንም ዉስብስብ ያልሆነ መንገድ ሲሆን በማደንዘዣ በመታገዝ በሽተኛዉ ምንም አይነት ህመም ሳይሰማዉ በ20 ደቂቃ ዉስጥ ራሱን አዉቆ ወደ ቀድሞ ጤንነቱ ይመለሳል፡፡
ከህክምናዉ በሁዋላ ልክ የወር አበባቸዉ በሚመጣበት ጊዜ እንደሚሰማቸዉ ያለ የሆድ ቁርጠት እና የሆድ መንፋት አይነት ስሜት ሊሰማቸዉ ይችላል፡፡ ይህንንም ስሜት ታይሌኖል (Tylenol) በመዉሰድ ማስታገስ ይቻላል፡፡
- ፅንስ የመፍጠር ሂደት
እንቁላል ከሴትዋ ማህፀን ከተወሰደ በሁዋላ በቀጥታ ወደ ላብራቶሪ ገብቶ እንዲዋሀድ ይደረጋል፡፡የእኛ አሰራር እንደተለመደዉ የአሰራር ሂደት እንቁላሉን እና የወንዱን የዘር ፍሬ ቀላቅሎ ያለመራባቱን ማየት ወይንም እስኪራቡ መጠበቅ ሳይሆን እያንዳንዱ እንቁላል ከወንዱ በተገኘዉ የዘር ፍሬ ቀላቅሎ ተዋህዶ እስኪፈጥር ድረስ በማክሮስኮፕ በመርፌ የወንዱን የዘር ፍሬ እንቁላሉን ወግቶ ማዋሃድ ነዉ፡፡የዚህ አይነቱ ተዋህዶ ኢንትራ ሳይቶፕላዝሚክ እስፐርም ኢንጄንክሽን (ICSI))ይባላል፡፡
ይህ ሲደረግ ጤነኛ የሆነ የወንዱ የዘር ፍሬ በ ማይክሮስኮፕ ተመርጦ ነዉ፡፡ተዋህዶዉም በሚቀጥለዉ ቀን በማክሮስኮፒክ ስር በማስቀመጥ ዘር መፈጠሩ ይረጋገጣል፡፡ዘር ከተፈጠረ በኋላም ለ5ቀናት ድረስ ብላሥቶሢት ደረጃ (blastocyst stage) እስኪደርስ ድረስ ማስፈልፈያ ማሽን ዉስጥ በማስቀመጥ የእድገት ሂደቱን እንከታተላለን
- ፅንስ ወደ ማህፀን የመመለስ ሂደት
ከአይቪኤፍ ሂደት በኋላ አንድ ወይም ሁለት ሽል (Embryo) ወደ ሴትዋ ማህፀን ሊመለስ ይችላል፡፡ይህም የሚወሰነዉ እንደ ፅንሱ ጤናማነት ፣ የታካሚዉ እድሜ እና ከአንድ በላይ እርግዝና ታካሚዉ ላይ የሚያመጣዉን ችግሮች በማጥናት ነዉ፡፡
ፅንስ የማዛወር ሂደቱ ህመም ስለማይኖረዉ ማደንዘዣ መጠቀም አስፈላጊ አይደለም፡፡ የተመረጠዉ ዘር አስፈላጊ ካልቸር ሚዲያ ባለበት (Culture media) ላይ እንዲቆይ ከተደረገ በኋላ በፅንስ መመለሻ ከቴተር (ET-catheter) በሚባለዉ ከትንሽ ካልቸር ሚዲያ ጋር የመመለሻ እቃ ተደርጎ በመዉሰድ በአልትራሳወንድ በመታገዝ ወደ ሴቷ ማህፀን እንዲመለስ ይደረጋል፡፡
ከፅንስ ዝዉዉር በሁዋላ ታካሚዋ ለ 15 ደቂቃ ያክል ዘና ብላ እንድትቆይ ይደረጋል፡፡ ከዛም በኋላ ወደ ቤትዋ በምትመለስበት ሰአት ከከባድ እንቅስቃሴ እና ለ 15 ቀናት ያክል የግብረስጋ ግንኙነት ከማድረግ መቆጠብ ይኖርባታል፡፡
የአይ.ቪ.ኤፍ (IVF) ህክምና መቼ መቋረጥ አለበት?
የአይ.ቪ.ኤፍ (IVF) ህክምና ለማቋረጥ ብዙ ምክንያቶ ሲኖሩት መቼ መቋረጥ እንዳለበትና ሌላ ምን አማራጭ መወሰድ እንዳለበት ለመወሰን ከሀኪሙ ጋር መመካከር ያሰፈልጋል፡፡